አጭር ነገር ለአንዳንድ ሙስሊም ወዳጆቼ !
አጭር ነገር ለአንዳንድ ሙስሊም ወዳጆቼ !
( ይህ መልዕክት የተዛባ እይታ ውስጥ ገብተዋል ብየ ላሰብኳቸው ውስን ሰዎች የተላለፈ ነው ብዙሐኑን አይመለከትም። )
በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ሂደት ላይ ታሪካዊው የነጃሽ መስጅድ ጉዳት እንደደረሰበት ተመልክተናል ይሄ እጂግ የሚያሳዝን ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካቶች ብስጭታችሁን ስትገልፁ ተመልክቻለሁ። እውነት ነው ለእምነቱ ቀናዒ የሆነ ሰው ቀርቶ ማንኛውም ሰው የተከበረው የአላህ ቤት ጉዳት ሲደርስበት ማዘኑ አይቀርም።
በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ሂደት በቀጠለበት ወቅት የአሸባሪው የትህነግ ቡድን አባላት ነገሮችን ለማወሳሰብ እና ስስ የሆነውን የሐይማኖት ጉዳይ መጫዎቻ ካርድ ለማድረግ የሐይማኖት ቦታዎችን ከለላ ለማድረግ እየተጠቀሙባቸው መሆኑን መረጃዎች እየወጡ ስንሰማ ነበር። ይህ ጉዳትም የዚያ ውጤት እንደሆነ አያጠራጥርም።
የእኔ ጥያቄ ?
አካባቢው በከባድ ጦርነት ውስጥ እንደመቆየቱ በመስጅዱ ላይ የደረሰውን ጉዳት ታስቦበት እንደተደረገ ( ታስቦበት ከሆነም ከትህነግ በላይ ሴረኛ የለም ! ) አድርጎ የተለየ ትርጉም መስጠት ተገቢ ነው ወይ ?
እንደ ሀገር በትህነግ ልክ የሌለው እብሪት ወደዚህ አላስፈላጊ የጠብ-መንጃ መፍትሔ ከመግባታችን በፊት ይህ አሸባሪ ቡድን በበርካታ ቦታዎች ለንፁሐን መገደል ተጠያቂ ነው። የሰሜን እዝ ወታደሮችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ታዲያ የዛሬው ዘመቻ የመስጅዱ ጉዳት ከሰብዓዊ ፍጥሮች በልጦ ነው ወይ የዛሬው ጩኸት ከፍየሏ በላይ የሆነው ?
በማይካድራ ፣ መተከል ፣ ጉራፈርዳ እንዲሁም በወለጋ ዛሬም ድረስ ያላባራ የንፁሐን አሰቃቂ ግድያ እንደቀጠለ ነው። የእነዚህ ንፁሐን ግድያ የተፈፀመባቸው ምክኒያት አማራ ስለሆኑ ብቻ ነው። ይህ ግልፅ የሆነ የዘር ማጥፋት ነው። ይህንን ኢሰበዓዊ ድርጊት ለምንድን ነው ማውገዝ የተሳነን ?
የአንዲትን ነፍስ በግፍ መገደል አቅልሎ የማይመለከተው እስልምና ውስጥ ሆነን ይህንን ግፍ የማናወግዘው ሰዎች ከመስጅድ ስለማይበልጡ ነው ? ወይስ የወጡበት አካባቢ ጠላት ስለሆነ ?
የምንጨነቀው ሐይማኖት መርጠን ከሆነ እና ሰብዓዊነቱን ከዘነጋነው እንኳን በመተከልም ሆነ በጉራርዳ እንዲሁም አንዳንዶቻችሁ እንደ ኢስላሚክ ስቴት በምትመፃደቁበት ኦሮሚያ ክልል በርካታ ሙስሊም አማራዎች በማንነታቸው ምክኒያት በግፍ ተገድለዋል። የእነዚህ ሰዎች ህይወትስ ከመስጅዱ ነው ወይስ በውስጡ ካሉት መቃብሮች ያነሰው ?
በጥቅሉ የፈረሰው መስጅድ በቀላሉ መታደስ ይችላል፤ ንብረትም ቢሆን ይተካል ! የሟች ነፍስ ግን ተመልሶ አይመጣም ! ሚዛናችን መሳት ግን ተገቢ አይደለም። ከእንዲህ አይነቱ የተዛባ አተያይ ወጥተን ተገቢ የሆነውን መንገድ አላህ ይምራን ስል መልዕክቴን እቋጫለሁ።
መልካም ቀን!
Tahir Mohammed